ፓራሜድ ኮሌጅ አርባምንጭ ለ17ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 300 ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መስኮች አስተምሮ በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር አያልቅበት ብርሀኑ ኮሌጁ ከተቋቋመበት ጀምሮ ላለፉት 17 ዓመታት ተማሪዎችን ተቀብሎ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ መርሐግብር እንዲሁም በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አሰልጥኖ በማስመረቅ ቀዳሚውን ስፍራ በመያዝ በዞናችን ብሎም በክልላችን ውጤታማ ተግባር እየፈጸመ ይገኛል ብለዋል።

እስከአሁን ድረስ ከአስራ አምስት ሺህ በላይ ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን ከ90 % በላይ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን በምርምር የተደገፉ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው በተጨማሪም በርካታ የበጎ ተግባራትን እየፈጸመ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኮሌጁ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ደረጃውን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ዶ/ር አያልቅበት ተናግረው ተመራቂዎች ለዛሬው በዓል ስኬት በድህነትና ችግር ያስተማራቸውን ህዝብ በቅንነትና በታማኝነት እንዲያገለግሉ አደራ ብለዋል።

የዕለቱ ክብር እንግዳ ፕሮፌሰር ይስሀቅ ከቼሮ የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪና መምህር ተማሪዎች በትምህርት ያገኙትን ዕውቀት በተግባር በማዋል ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለሀገራቸው ለውጥ መትጋት እንዳለባቸው በማሳሰብ ሥራ ጠባቂ ሣይሆኑ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ መክረዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት በተማሩት የሙያ መስክ በታማኝነትና በትጋት ከመሥራት ባለፈ ለሀገሪቱ ሰላምና ብልጽግና የበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ከምረቃ ሥነ-ሥርዓት ጎን ለጎን የምረቃ ቀንን ምክንያት በማድረግ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብርም ተካሂዷል።

በመጨረሻም የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።