በመሪሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ም/ኃላፊና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሀላፊ አቶ ወንድማገኝ ታዬ ኮሌጁ በሀገር ወዳድና በሀገር በቀል ኢንቨስተሮች የተቋቋመ መሆኑን ጠቅሰው ከሌላው ለየት የሚያደርገው “ያገኘውን ገንዘብ እዚሁ ለትምህርት ኢንቨስት ማድረጉ ነው” ብለዋል።

በክልሉ ከሚገኙ የትምህርት ተቋማት ከዲፕሎማ ጀምሮ እስከ 2ኛ ዲግሪ ድረስ በማስተማር አንጋፋ ተቋም በመሆኑ አመስግነዋል።

ተቋሙ ከመማር ማስተማር ሥራው በተጨማሪ በምርምር ላይ የተመሠረተ ከፍተኛ የማህበረሰብ አገልግሎት ለህብረተሰቡ እየሰጠ መቆየቱን አውስተው ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ (CPD) ሥልጠና ለመስጠት ዕውቅና አግኝቶ በዛሬው ዕለት ሥራውን በይፋ መጀመሩ እጅግ በጣም የሚያስደስት ነው ብለዋል።

ለጤና ባለሙያዎች ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ (CPD) ስልጠና ማግኘት የሙያ ፈቃዳቸውን ለማደስ የሚያስችላቸው ሆኖ ስልጠናውን ሳይቸገሩ በአቅራቢያቸው አግኝተው ለህብረተሰቡ ብቁ የጤና አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችላቸው መሆኑን አቶ ወንድማገኝ ገልጸዋል።

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር አያልቅበት ብርሃኑ ፓራሜድ ኮሌጅ በአገራችን ካሉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንጋፋ ሆኖ በመቆየት ላለፉት 17 አመታት ተማሪዎችን ተቀብሎ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አሰልጥኖ በማስመረቅ ቀዳሚውን ስፍራ በመያዝ በዞናችን ብሎም በክልላችን ውጤታማ ተግባር እየፈጸመ ይገኛል ብለዋል።

ኮሌጁ ከተቋቋመበት ከ1999 ዓ/ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ በቅድመ-ምረቃ፣ድህረ-ምረቃ እና በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ በአጠቃላይ ከዘጠኝ ሺህ በላይ ተማሪዎችን ያስመረቀ መሆኑና ከ90% በላይ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን ለመጠበቅ በትምህርት ሚኒስቴር በ2015 ዓ/ም ተማሪዎች በከፍተኛ ተቋም ያገኙትን አጠቃላይ የትምህርት ደረጃን ለመገምገም የተዘጋጀውን የመውጫ ፈተና በማስፈተን በአገር አቀፍ ደረጃ ካሉት 366 ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከ50% በላይ በማሳለፍ ውጤት ካዝመዘገቡ ከ17 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

ተቋሙ ከመማር ማስተማር ስራው ባሻገር የህብረተሰቡን ችግር መሠረት ያደረጉ ጥናቶችን በማጥናትና ውጤታማ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ እየተገበረ እንደሚገኝ ዶ/ር አያልቅበት አስረድተዋል።

ኮሌጁ ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ከጤና ሚኒስቴር ባገኘው ፈቃድ መሠረት የጤና ባለሙያዎች የሞያ ፈቃድ ማደስ የሚያስችል ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ (CPD) ስልጠና ለመስጠት ማዕከል በመክፈት በዛሬው ዕለት ሥራውን በይፋ የጀመረ መሆኑን አብስረዋል።

ኮሌጁ በዚህ አመት ስለ ስነተዋልዶ ጤና፣ የህይወት ክህሎት ስልጠና፣ ለተማሪዎች ለፈተና ዝግጅት የሚረዳቸው እና ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ስሄዱ የሚያጋጥማቸው ተግዳሮቶች እንዴት መቋቋም እንዳለባቸው በአርባምንጭ ከተማ ባሉ 2ኛ ደረጃ ትም/ት ቤቶች ይሰጥ የነበረውን ስልጠና አሁን ላይ አድማሱን በማስፋት አቅራቢያ ባሉ ዞኖች ላይ በሰፊው እየሰጠ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በቀጣይ ኮሌጁ ከክልልና ዞኖች ጤና ተቋማት ጋር የተጠናከረ ትስስር በመፍጠር የጤና አገልግሎትን ጥራት ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራም ዶ/ር አያልቅበት ተናግረዋል።

የጤና ባለሙያዎች በዚህ በተፈጠረው ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ (CPD) ስልጠና ሳይቸገሩ በአቅራቢያው እንዲያገኙ ሆኖ በዚህም ዕውቀታቸውንና ክህሎታቸውን በማሻሻል ለአከባቢው ማህበረሰብ የበለጠ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚረዳ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ (CPD) ስልጠና ማስጀመሪያ መሪሃ ግብር ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሀላፊ አቶ ወንድማገኝ ታዬ፣የኮሌጁ ዲን ዶ/ር አያልቅበት ብርሃኑ፣የጋርዱላ ዞን፣የአሌ፣የቡርጂ፣የኮንሶ፣የኮሬ፣የባስከቶ፣የጎፋ፣የደቡብ ኦሞና የአሪ ዞኖች ጤና መምሪያ የሰው ሀብት ልማት አስተዳደር ቡድን መሪዎች እና የኮሌጁ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።