ፓራሜድ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 1ሺህ 450 ተማሪዎች አስመረቀ

ተመራቂ ተማሪዎችም ለሀገሪቱ ሰላምና ብልጽግና የበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በእለቱ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኮለጁ ዲን አቶ ገረሱ በየነ እንዳሉት ተመራቂዎች እራሳቸውን ሆነው ጠንክረው ከሰሩና ታማኝ ከሆኑ ስኬታማ ከመሆን የሚያግዳቸው አንዳች ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።

ተማሪዎች በትምህርት ያገኙትን ዕውቀት በተግባር በማዋል ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለሀገራቸው ለውጥ መትጋት እንዳለባቸው ያሳሰቡት ዲኑ ሥራ ጠባቂ ሣይሆኑ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑም መክረዋል።

ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እና ከክልሉ ቴ/ሙ/ት/ስ ቢሮ ባገኘው ዕውቅና መሠረት በሁለት የማስትሬት ዲግሪ በ13 ዲግሪ መርሃ ግብርና በቴኒክና ሙያ በደረጃ 4 በዲፕሎማ ፕሮግራሞች እያሰተማረ ይገኛል ።

ኮሌጁ በዛሬው ዕለት በቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና በደረጃ 4 በዲግሪ መርሃ ግብር እንዲሁም በማስተር መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 450 ተማሪዎችን አስመርቋል።

የዕለቱ ክብር እንግዳና የእርባምንጭ ዩኒበርሲቲ ፕረዝዳንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ትምህርት ለአንድ ሀገር ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው ተማሪዎች ያገኙትን ዕውቀት በተግባር በማስደገፍ ለሀገራችን ብልጽግና መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ዶ/ር ዳምጠው አክለው ኮሌጁ ከምንም በላይ ለትምህርት ጥራት በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አሳስበው አርባምንጭ ዩንቨርሲቲ በአከባቢው ያሉ ከፍተኛ ተቋማትን በመደገፍ አብሮ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

በዕለቱ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ተመራቂ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት በተማሩት የሙያ መስክ በታማኝነትና በትጋት ከመሥራት ባለፈ ለሀገሪቱ ሰላምና ብልጽግና የበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።